በዘመኑ ህልፈት በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት አምጻኤ ዘመናት ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ዮሓንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም በጤና አሸጋገረን፡፡
ያለፈው ዘመን 2012 ዓ/ም ለሰው ልጆች በጎ ዘመን አልነበረም፡፡ የኮሮና ቫይረስ ዓለምን ያስጫነቀበት፣ የሰው ልጆችን ህልውና የተፈታተነበት፣ ሰውም አቅሙን (ልኩን) ያወቀበት ዘመን ነበር፡፡
ዛሬ አዲስ ዓመት ለመቀበል ዋዜማዋ ላይ ላለን ኢትዮጵያውያን ደግሞ ችግሩ በጆሮ ላይ ደግፍ ሆኖብን ነበር፡፡ ለሀገር ፍቅር፣ ለወገን ክብር የሌላቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆነ ክፉ የክፉ ጥፋት ልጆች እነ ሆድ አምላኩ ከመቼውም የከፉበት፣ ንፁሓን የተገፉበት፣ ክርስቲያነኖች ከእንስሳ ባነሰ ክብር የተገደሉበት፣ የታረዱበት ዘመን ነበር፡፡
በአጠቃላይ 2012 ዓ/ም ሀገርና ቅድስት ቤተክርስቲያን የመከራ ቁና የተሸከሙበት የክፉዎች ዘመን ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን 2012 ዓ/ምን ዘመነ ሰማዕታት ብላ ልትሰይመው ይገባል፡፡ እርግጥ ነው መከራ ለክርስቲያን ጌጡ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ስንመታ እንደ ሚስማር የምንጠብቅ ስለንፅህት ሃይማኖታችን መከራ ስንቀበል ብንደሰት እንጂ በመከራ እንደማንሳቀቅ ጠላት ይወቅ ይረዳ፡፡
ዛሬ ያ ዘመን አርጅቷል፡፡ አዲስ ዘመን ልንቀበል ዋዜማው ላይ ነን፡፡ ያ ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን 2013 ዓ/ም መጥቷል፡፡
ስለዚህ የአህዛብን ፈቃድ ያደረግንበት፣ የሴይጣንን ሥራ የሠራንበት ያለፈው ዘመን ይበቃል፡፡
ክፉዎች፡-ሀገር ያመሳችሁበት፣ ንብረት ያወደማችሁበት፣ ቤተክርስቲያን ያቃጠላችሁበት፣ ሰውን ያስለቀሳችሁበት፣ ሰውን ያፈናቀላችሁበት፣የሰውን ደም ያፈሰሳችሁበት፣ የገደላችሁበት ዘመን ይበቃልና በአዲስ አስተሳሰብ በአዲስ አእምሮ አዲስ ሰው ሆናችሁ አዲሱን ዘመን ተቀበሉ፡፡
ክርስቲያኖች፡-ቤተክርስቲያናችሁ የተቃጠላችበት፣ የተሰዳዳችሁበት፣ የተገረፋችሁበት፣ ያለቀሳችሁበት፣ የተገደላችሁበት ያ የመከራ ዘመን ያ ያለፈው ዘመን ይበቃልና እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጋችሁ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ አእምሮ አዲሱን ዘመን ዘመነ ማቴዎስን ተቀበሉ፡፡
ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ፍቅር የነገሰበት ዘመነ ሰላም፣ ዘመነ ፍስሃ ያድርግልን ፡፡ አሜን